You are here

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ለአራተኛ ጊዜ 28 ቀናት ቀጠሮ ተሰጠባቸው

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ የሚገኙት የሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀጠና/ዞን አመራሮች ለአራተኛ ጊዜ 28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጠባቸው፡፡
ዛሬ ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የቀረቡት የሰማያዊ (የፓርቲው የጎንደር አደራጅ አቶ አግባው ሰጠኝ)፣ የአንድነት እና መኢአድ የዞን አመራሮች ፖሊስ ‹‹ምስክሮችን ማደራጀት ይቀረኛል›› በሚል ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆ ለአራተኛ ጊዜ ፍርድ ቤቱ 28 ቀናት ሰጥቷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በጎንደርና ጎጃም አካባቢዎች የዛሬ ሦስት ወር በፖሊስ ታስረው ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ እንዲዛወሩ የተደረጉ ሲሆን፣ በማዕከላዊ ምርመራ ማዕከል ከፍተኛ ድብደባ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የተጠርጣሪ ወዳጆች ተጠርጣሪዎቹን እንዳይጠይቁ አሁንም ድረስ እንደተከለከሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

‹‹ፖሊስ የሰነድ ምርመራውን በማጠናቀቁ ምንም ሊሰራው የሚችለው ተጨማሪ ስራአልቀረውም›› ያሉት የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ ገበየሁ፤ የፓርቲ አመራሮቹ ለተጨማሪ 28 ቀናት ማዕከላዊ እንዲቆዩ ፍርድ ቤቱ መፍቀዱ ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው የጊዜ ቀጠሮ መሰረት አመራሮቹ የካቲት 17 ቀን 2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡