You are here

ሰማያዊ በመጀመሪያ ቀን ጠ/ጉባኤ ውሎው የሦስት ዓመት ሪፖርቶችን አዳመጠ

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ እያካሄደ የሚገኘው ሰማያዊ ፓርቲ በመጀመሪያ ቀን ውሎው የፓርቲውን የሶስት ዓመት የብሄራዊ ምክር ቤት፣ ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን እንዲሁም የሂሳብ ሪፖርቶችን አዳምጦ ውይይት አድርጓል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ነሀሴ 16 እና 17/2007 ዓ.ም ጉባኤውን ለማድረግ በያዘው ፕሮግራም መሰረት ዛሬ በመክፈቻው ዕለት የፓርቲውን የሶስት አመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርቶችን ለጉባኤው በማቅረብ ውይይት ያደረገ ሲሆን፣ ሰማያዊ ባለፉት ሶስት አመታት ያከናወናቸውን ተግባራት አውስቷል፡፡ ፓርቲው ራሱን በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ ስራ እንደሰራ በመጥቀስ፣ አደረጃጀቱን በማስፋት በኩል ግን ውስኑነቶች እንደነበሩበት በጉባኤው ላይ ተመልክቷል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 25/2005 ዓ.ም ከስምንት አመታት በኋላ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ህገ-መንግስታዊ መብት በማስመለስ ሰልፉን በአዲስ አበባ ማድረጉ ፓርቲው ካከናወናቸው ተግባራት መካከል በአብይነት ተወስቷል፡፡ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ጉባኤተኞችን ያሳተፈው ይህ ጉባኤ በነገው ዕለትም ቀጥሎ ይውላል፡፡

በነገው ውሎውም የፓርቲውን ሊቀመንበር፣ የብሄራዊ ም/ቤት እና የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን አባላትን ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡