You are here

ሰማያዊ ፓርቲ የዞን ዘጠኝ አክቲቪስቶችንና ሌሎች ጋዜጠኞች ላይ እየተደረገ ያለውን እስር አጥብቆ ያወግዛል!

በነገው ስልፍም ይፈቱ ዘንድ ድምጹን ያሰማል!

ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹የተነጠቁ መብቶቻችን እናስመልሳለን›› በሚል ሚያዝያ 19 ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ከምናነሳቸው ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሰልፉ ገዥው ፓርቲን ላይ የሠላ ትችት ስለሰነዘሩና ለህዝባቸው መረጃ ስለሰጡ ብቻ የሚደርስባቸውን ህገ ወጥ እርምጃ ያወግዛል፡፡

በሳምንቱ ውስጥ የህዝብን መብት ለማስመለስ ለጠራነው ሰልፍ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ 50 ያህል አመራሮችና አባላት በህገ ወጥ መንገድ ታስረዋል፡፡ በትናንትናው ዕለት የፓርቲያችን ሊቀመንበር (ማታ ተፈትተዋል)፣ ምክትል ሊቀመንበር፣ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በህገ ወጥ መንገድ መታሰራቸው ይታወቃል፡፡ በተመሳሳይ ወቅት የዞን ዘጠኝ አክቲቪስቶችና ሌሎች ጋዜጠኞችም ታስረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ሌሎችን ለማሰር ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ይህን የገዥው ፓርቲ ከፍርሃት የመነጨ አምባገነናዊ እርምጃ በጽኑ ይቃወማል፡፡ በነገው ዕለትም በእነዚህ አክቲቪስቶችና ጋዜጠኞች ላይ የተደረገውን እስር የሚያወግዝ መሆኑን መግለጽ ይወዳል፡፡

ኑ ራሳችን ነጻ በማውጣት የአገራችን እጣ ፈንታ እንወስን!